
የሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነትን በተግባቦትና ህዝብ ግንኙነት ስራዎች ውጤታማ ማድረግ የሚያስችል ፎረም ተቋቋመ።
ፎረሙ በቃል ኪዳኑ መሰረት ስርዓተ ምግብ እና ጤናን በማሻሻል ከሁለት ዓመት በታች የህፃናት የመቀንጨር ችግርን በ2022 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት የሚደረገውን ሐገራዊ ጥረት በተግባቦት እና ህዝብ ግንኙነት ስራዎች ለማገዝ ያለመ ነው ተብሏል።
የጤና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ተገኔ ረጋሳ የሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት በተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በቅንጅት እየተሰራበት መሆኑን ተናግረዋል።
የቃል ኪዳኑን ግብ ከዳር ለማድረስም በምግብና በስርዓተ ምግብ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የተግባቦትና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ሚና የላቀ መሆኑን ገልፀዋል።
የመቀንጨር ችግር በሀገር ደረጃ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስና የባህሪ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ ጠንካራ የተግባቦት ስራዎችን በተቀናጀ መልኩ መከወን እንደሚገባ ጥሪ መቅረቡን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
