
ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ የአማራ ክልል ተፈናቃዮች ከዛሬ ጀምሮ ወደ ቀያቸው መመለስ ይጀምራሉ።
እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ሁሉንም ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ለመመለስ በተያዘው እቅድ መሰረት ከተለያዩ አካባቢዎች በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው የመመለሱ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
የአማራ ክልልም በመጠለያ እና ቤተዘመድ ጋር የሚገኙና የእለት ድጋፍ ብቻ እየተደረገላቸው ያሉ ተፈናቃዮችን ከየመጡበት ክልል አመራሮች ጋር በመወያየት እንዲመለሱ እያደረገ መሆኑን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ መላኩ አለበል ተናግረዋል።
በዚህም ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች ከዛሬ ጀምሮ ወደ ቀደመ ቀያቸው ይመለሳሉ።
11 ሺህ 900 የሚሆኑት እነዚህ ተፈናቃዮች ከምስራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ እና ጅማ ዞኖች እንዲሁም ቡኖ በደሌ የተፈናቀሉ ናቸዉ።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እታገኘሁ አደመ፥ ተፈናቃዮቹን ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ለመመለስ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።
የመመለሱ ስራም በየአካባቢዎቹ ሰላም መኖሩ ተረጋግጦ እንዲሁም ሁኔታዎች ተመቻችተው መሆኑን ጠቅሰው፥ የመመለስ ስራው ፍላጎትን መሰረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በመላ ሀገሪቱ 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ተፈናዮች የነበሩ ሲሆን አሁን ላይ በርካቶቹ ወደ ቀያቸው መመለስ ጀምረዋል።
