
ለመጀመሪያ ጊዜ 4 የእንግሊዝ ክለቦች በአውሮፓ ሁለት ታላላቅ የውድድር መድረክ ላይ ለፍጻሜ የሚቀረቡ ሲሆን ትላንት ምሽት በዮሮፓ ሊግ አርሰናል ከሜዳው ውጪ ቫለንሺያን እንዲሁም ቼልሲ በሜዳው ኢንትራፍራንክፈረትን አሸንፎ በዮሮፓ ሊግ ፍጻሜ ደርሰዋል፡፡ ቀደም ብለው ሊቨርፑል እና ቶተነሃምም ድራማዊ በሆነ ክስተት ለቻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ መድረስ መቻላቸው ይታወሳል፡፡
ቶተነሃም ሊቨርፑል ቼልሲ እና አርሰናል በቻምፒዮንስ ሊጉ እና በዮሮፓ ሊጉ ፍጻሜ ጨዋታዎች ላይ በመሳተፍ አዲስ ታሪክ መስራት ችለዋል፡፡
ከዚህ በፊት በ1971-72 የውድድር ዘመን በዩኤፋ ካፕ የፍጻሜ ጨዋታ ቶተነሃም ዎልቭስ ያስተናገደበት እንዲሁም በ2007-08 በቻምፒዮንስ ሊግ ማንችስተር ዩናይትድ ከቼልስ ካደረጉት የፍጻሜ ጨዋታ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ 4 የእንግሊዝ ክለቦች በአውሮፓ በሁለት የውድድር መድረኮች ላይ ለፍጻሜ ደርሰዋል፡፡
ስፔን በ2015-16 የውድድር አመት ሶስት ክለቦች በሁለት የአውሮፓ ታላቅ መድረክ ላይ የፍጻሜ ተፋላሚ ሲሆኑ በቻምፒዮንስ ሊጉ ሪያል ማድሪድ ከአትሌቲኮ ማድሪድ፤ በዩሮፓ ሊግ ደግሞ ሲቪያ ከሊቨርፑል ጋር ጨዋታቸውን አከናውነው በአናይ ኤምሬ ሲቪያ አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
የዮሮፓ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ አርሰናል ከቼልሲ በአዘርባጃን ባኩ ግንቦት 21 የሚደረግ ሲሆን ሊቨርፑል ከቶተነሃም ግንቦት 25 በስፔን በአትሌቲኮ ማድሪድ ሜዳ ዋንዳ ሜትሮፖሊታኖ ስታዲየም ይካሄዳል፡፡
